የቤል መርገጫ አልባው እንጦርጦስ- ቻርተር ከተማ

የቤል መርገጫ አልባው እንጦርጦስ- ቻርተር ከተማ

To Read in PDF

ሁሉም ሰው በህይወቱ እንዳለው ዓይነት ምኞትና የሚፈልገውን ለማግኘት የተጋረጠው ጋሬጣ የመጋፈጥ ጥረቱ በፖለቲካም ውስጥ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ የመንግስት መመሪያና ህጎች መስራት የምንችለውን ይገድቡናል፡፡ እኚያ ግን በስልጣኑ ወንበር ላይ ያሉቱ ከሌሎቻችን ይለያሉ፡፡ እነሱ ስለራሳቸው ጥቅም ህግን ማርቀቅ ይችላሉ ከዚያም የሚፈልጉትን ለማግኘት ሁሉ ቀላል ይሆንላቸዋል፡፡ የሰዎችን ፍላጎትና ፍላጎታቸውን እንዴት እንደሚያገኙት ያለን የመረዳት መጠን እኛያ ስልጣን ላይ ያሉቱ ስለምን ብዙው ጊዜ ጎጂ ድርጊቶችን እንደሚፈፅሙ ለማስረዳት ረዥም አቅም ይኖረዋል፡፡ እዚህ ላይ የፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ብሩስና ኤልስተር ‘የአምባገነን ድርሳን’ ባሉት መጽሐፋቸው ላይ ያሰፈሩትን የአሜሪካዋ ትንሽ ከተማ ቤል ትረካ እንጥቀስ፡፡ በትረካቸው የትንሿ ከተማ ቡድን ስቁንቁንነት፣ ለሀብት መስገብገብ፣ ንፉግነትና ምግባረ ብልሹነት፤ በመሪዎች ዕይታ ዓለም ምን እንደምትመስል ለማድነቅ ይጋብዘናል፡፡

ይህ ታሪክ የግለሰቦች ግላዊ ታሪክ ሳይሆን የፖለቲካ ታሪክ መሆኑን ማስታወስ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ውይይታቸን ስለቡድን ሙስና፣ ስለስልጣን የኑዛዜ ውርርስ ሆነ ሌላው፤ ዋናው ነገረ ጉዳይ የስልጣን ጥቅም እንዴት እንደሚገኝና እንደሚጠበቅ የሚያውቁትና የሚረዱት እነዚህ ሰዎች መሆናቸው ነው፡፡ ግና ብዙም ሳንቆይ የትንሿ ከተማ የአኗኗር ጸባይ ታሪክ በእያንዳንዱ የፖለቲካና የድርጅቶች አስተዳደር ደረጃዎች ውስጥ እንደሚደጋገም እንረዳለን፡፡ ያኔም ካልተለመደው የካሊፎርኒያዋ ቤል ታሪክ ውስጥ ከተለመደው ውጪ የሆነ ምንም እንደሌለ እንገነዘባለን፡፡

36 ሺህ ገደማ የህዝብ ብዛት ያላት ትንሿ ከተማ የቤል የቀድሞ የከተማ ስራ አስኪያጅ ሮበርት ሪዞ ይባላል፡፡ ቤል ድህነት ያቆዘማት የሂስፓኒክና ላቲኖ መኖሪያ የሆነች የሎሳንጀለስ ዳርቻ ነች፡፡ የካፒታል ገቢ ምጣኔዋ (የነፍስ ወከፍ) ከ10ሺ-25ሺ የሚዋዥቅ ሆኖ ከካሊፎርኒያም ሆነ ከሀገሪቱ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ በታች ነው፡፡ የከተማዋ ሲሶ በላይ ታታሪ ሰራተኞች (ነዋሪዋች) ከድህነት ጠለል በታች ይኖራሉ ህይወት በቤል ቀላል አይደለም፡፡ የከተማዋ የለውጥ ስኬቶችና መጻኢ ዕድሎች ገና የህብረተሰቡ ኩራትና ሸክሞች ናቸው፡፡ ከብዙ ችግሮቿ ጋር እየተጋፋች ቢሆንም እንኳ ህብረተሰቧ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ በማድረግና ንብረቱን ከቀማኛ በመጠበቅ ከካሊፎርኒያ ሌሎች ህብረተሰሰቦች አማካይ የበለጠ ብቃቷን በተደጋጋሚ አሳይታለች፡፡

ሮበርት ሪዞ የከተማዋ ስራ አስኪያጅ የነበረባቸውን 17 ዓመታት በኩራት ወደኃላ በእርግጠኝነት እንደሚያስታወሳቸው ማመን አይከብድም፡፡ በ2010 በዚያን ጊዜ የቤል ከንቲባ የነበረው ኦስካር ኸርናንዴዝ (በኃላ በሙስና ዘብጥያ ተወርውሯል) ስለ ሪዞ እንዲህ ብሎ ነበር፡- በ1933 ሪዞ (እርሱም በመጨረሻ በሙስና ተከስሷል) ሲቀጠር ከተማዋ የውድቀት አፋፍ ላይ ነበረች ለ15 ተከታታይ የሪዞ የመሪነት ዘመናት (በ2010 ከስልጣኑ እስከወረደበት ድረስ መሆኑ ነው) የከተማዋ በጀት የተመጣጠነ (balance) ነበር፡፡ ሪዞ ከተማዋ እዳዋን ከፍላ ገንዘብ ሊተርፋት የምትችል (solvent) ስላደረጋትና በዛው እንድትቀጥል ስለረዳት ኸርናንዴዝ ገለታን አብዝቶለታል፡፡

ፊት ለፊት ከሚታየው አስደሳች ገጽ በስተጀርባ ቅሉ ፖለቲካ በእምነት እንዴት እንደሚሰራ የሚገልፅ ታሪክ ይገኛል፡፡ ተመልከቱ ሮበርት ሪዞ በ1993 ሲቀጠር ዓመታዊ ደመወዙ 72,000 ዶላር ነበር 17 ዓመታት በስልጣን ከቆየ በኋላ ከስልጣኑ ተገዶ በ2010 ክረምት ላይ እንዲወርድ ሲደረግ የስልጣኑ ጊዜ ያገኘው የነበረው ዓመታዊ ገቢ 787,000 ዶላር ነበር፡፡

ይህን በንፅፅር እናስቀምጠው፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ደመወዝን አጉኖታል ቢባል እንኳ በ2010 ሊያገኝ የሚገባው 108,000 ዶላር ይሆን ነበር፡፡ የእርሱ ግን ሰባት እጥፍ!! ዝቅተኛ የዋጋ ግሽበት በተመዘገበባቸው ረዥም ዓመታት የእርሱ ደመወዝ በዓመት 15% ዓመታዊ የወለድና ዋና ጥርቅም ማባዣ (compound rate) አሳይቷል፡፡ ከሌሎች የመንግስት ኃላፊነት ላይ ካሉ ባለስልጣናት አንፃር እንዴት ነው የከተማ ስራ አስኪያጁ ሪዞ ይህን ያህል ሊከፈለው የቻለው? የአሜሪካ ፕሬዝዳንት 400,000 ዶላር ይከፈለዋል፡፡ የካሊፎርኒያው ገዥ ከ200,000 ብዙም አይበልጥም፡፡ ከቤል በትንሽ ፍንጥር እርቀት ላይ የሚገኘው የሎስአንጀለሱ ከንቲባ የሚከፈለው ከ200,000 ትንሽ የሚበልጥ ነው፡፡ እርግጠኛ ለመሆን ሮበርት ሪዞ በካሊፎርኒያ ከፍተኛ ተከፋይ የሆኑት የመንግስት ሠራተኞች እንኳ የሚጠጉት አልነበረም፡፡ በዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ከፍተኛው ተከፋይ የከተማ ስራ አስኪያጅ እንዳልነበረ መናገር ይቻላል (ወይም ቢያንስ ሌላ ቤል እስክናገኝ ድረስ)፡፡

ስለዚህም የብዙዎች ተፈጥሮአዊ አሳብ ሊሆን የሚችለው ሮበርት ሪዞ የግድ የገንዘብ ዘርፏል ወይም በታወቀ ዝናው በመጠቀም የጣፋጩን ማሰሮ እየሞላ ነበር ወይም ለእሱ ተገቢና ህጋዊ ያልሆነ የገንዘብ ምንጭ ወደራሱ አዙራል፡፡ አሊያም ምናልባት ቢያንስ የሆነ ህጋዊ ያልሆነና ከስነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት አድርጓል፡፡ የዲሞክራቶች ለገዢነት እጩ ተወዳዳሪ የነበረ ዋና አቃቢ ህግ ጄሪ ብራውን በ2010ሩ የቤል ቅሌት ወቅት የተጣሰ ህግ ካለ ለመመርመርና ለመፈለግ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ የንግግሩ ትርጉም ግልፅ ነበር ማንም ለትንሽ ከተማ ስራ አስኪያጅ 800,000 በዓመት አይከፍልም፡፡ እውነታው ቅሉ ትንሽ የተወሳሰበ ነበር፡፡ ትክክለኛው ታሪክ ግን በፖለቲካ ብልጣብልጥነት (ለወቀሳ የተተወ) የቤል ድምፅ ሰጪዎችና እነርሱ የሚወክሉት የከተማው ምክር ቤት አባላትን በዘዴ ግልፅ የሆነ ዕቀባ እንዲኖር በማድረግ ሲሆን ብቸኛው አጋዣቸው በሌብነት መነካካት ነው፡፡

ከቤል ጋር የሚነፃፀሩ ከተሞች በአማካይ ለምክር ቤት (ካውንስል) አባላት 48,000$ በዓመት ይከፍላሉ፡፡ ከአምስቱ የቤል ካውንስል አባላት 4ቱ ወደ 100,000$ የሚጠጋ ዓመታዊ ክፍያ ያገኛሉ፡፡ ዘዴው ቀላል ነው፡፡ የካውንስል ደመዎዛቸው ብቻ ሳይሆን በየወሩ ወደ 8,000 ዶላር የሚጠጋ (በዓመት 96,000 ዶላር) የከተማው ኤጀንሲ ቦርድ አባልነት ክፍያ ይሰጣቸዋል፡፡ ምስኪኑ የካውንስሉ አባል ሎሬንዞ ቪሌዝ ብቻ ይሄን ሽልማት ማጨድ አልቻለም፡፡ ቬሌዝ በግልፅ 8,076 $ በዓመት በካውንስል አባልነቱ የሚያገኘው ብቻ ነው፡፡ የካውንስል አባላት ጓደኞቹ በየወሩ ከሚያገኙት ጋር እኩል የሆነ፡፡ ያልተመጠነ ደመዎዝና ጡረታ ለአቶ ሪዞ ብቻ ሳይሆን ለረዳት የከተማው ስራ አስኪያጅና ለቤል ዋና ፖሊስ (ኮሚሽነር) የሚሰጡት እነዚህን አለመመጣጠን እንዴት መግለፅ ይቻላል? መልሱ የሚያርፈው በብልጠት ከሚካሄደው የምርጫ ጊዜ ላይ ይሆናል፡፡ የከተማው መሪዎች ስልጣን ለመያዝና ማካካሻ ክፍያቸውን ለመመደብ ጥቂት ድምፅ ሰጪዎች ላይ እንደሚወሰኑ አረጋግጠዋል፡፡ ምስኪኑ ህዝብ ለከተማው መሪዎች እንዴት አስደስተው እንደሚሸልሟቸው ለማየት ከ2005 ልዩ ምርጫ መነሣት ይኖርብናል፡፡ ምርጫው ከተማዋን ‘ከአጠቃላይ ከተማነት’ ወደ ‘ቻርተር ከተማነት’ የቀየሩበት ነው፡፡ ምናልባት በአጠቃላይ ከተማነትና በቻርተር ከተማነት መሐል ያለው ልዩነትና ክፍተት ምንድነው?ብለው መጠይቅዎ አይቀር ይሆናል፡፡ ግልፅ የሆነው መልሱ ቀንና ሌሊት ነው፡፡ በአጠቃላይ ከተማ ውሳኔዎች በግልጽ በቀን ብርሃን ሲወሰኑ በቻርተር ከተማ ግን ብዙውን ጊዜ በሚስጥር በተዘጋ በር ውስጥ ነው፡፡ የአጠቃላይ ከተማ የሚገዛበት ህግ በክልሉ ወይም በፌዴራል ህግ ሲሆን ቻርተር ከተማ አስተዳደር የሚገዛው እርስዎ እንደሚገምቱት በከተማዋ ቻርተር ነው፡፡

የካሊፎርኒያ ህግ አውጪዎች በ2005 የጄኔራል ከተማ የካውንስል አባላት ደመወዝ ለመገደብ ወስነው ነበር፡፡ በዛው ዓመት ብልጣ ብልጦቹ ታዋቂ የቤል ፖለቲከኞች በሮበርት ሪዞ መሪነት አምሮታቸውን የሚሸፍኑበት መንገድ አገኙ፡፡ በአምስቱ የካውንስል አባላት ድጋፍ ቤልን ወደ ቻርተር ከተማነት ለመቀየር ልዩ ምርጫ ተሰናዳ፡፡ ወደ ቻርተር ከተማ የመመንዘር ዓላማው ከተማዋን ከክልል ባለስልጣናት ከርቀት ከሚሰጥ ውሳኔ አላቆ የራስን አገዛዝ ነፃነት ከፍ ለማድረግ ነበር፡፡ የአካባቢ ባለስልጣናት ለህዝባቸው የሚጠቅመው በማወቅ በርቀት ከህብረተሰቡ ጋር ቁርኝት ሳይኖራቸው ከሚሾሙ ፖለቲከኞች የተሻሉ ናቸው፡፡ ወይንም ቢያንስ የቤል መሪዎች ካሊፎርኒያን ሞግተውበታል፡፡

የሸገርና የድሬ ታሪክ

አስቀድመን እንዳልነው ካልተለመደው የካሊፎርኒያዋ ቤል ታሪክ ውስጥ ከተለመደው ውጪ የሆነ ምንም እንደሌለ ሃገራችንም ታስገነዝበናለች፡፡ በሃገራችን ሁለት በቻርተር (ህገመንግስት) የሚተዳደሩ ከተሞች አሉን፡፡ አዲስ አበባና ድሬዳዋ፡፡ አዲስ አበባ ክልል 14 ተብላ የኖረች ብትሆንም’ኳ በአንድ የምትታሰርበት የብሔር ገመድ በመጥፋቱ ለብዙሐንነቷ ቻርተር ከተማነት ይገባታል ተብሎ ቻርተር ተረቀቀላት፡፡ እናም ሕዝቦቿ ራሳቸውን በራሳቸው ሊያስተዳድሩ ተለዩ፡፡ እንደ ቤል ብልጣብልጥ ፖለቲከኞች ከራስ ጥቅም፣ ቂም በቀልና ጥላቻ ያልጸዱት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሲያዩት ደስ የሚያሰኝ (ሕዝቦች ሉዓላዊ ሁነው ራሳቸውን መርጠው ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት ሥርዓት ይመስላልና) ውስጡ ግን የሥልጣን እድሜ ማርዘሚያ፣ እግራቸውን ከድንበር እስከ ድንበር የሚያዘረጋ ንቀት የሞላው (ሕዝቦች መሪዎቻቸው ከራሳቸው የሚመረጡ ሳይሆን ለእነሱ የሚያውቅላቸው ምስለኔ የሚሾምላቸው ሕዝቦች አድርጓቸዋልና) ቻርተር አረቀቁ፡፡

ቻርተር ከተማነት ግን ብርቋ አይደለም፡፡ ከ1966 ዓ.ም በፊት አዲስ አበባ በከንቲባ (lord-mayor) የሚመሩ ቻርተር ከተሞች ከነበሩት ጥቂት የኢትዮጵያ ግዛቶች አንዷ ነበረች፡፡ ከንቲባውም ከፖለቲካዊ ቁጥጥር በብዙ ነጻ የሆነ በመሆኑ ሉዓላዊነት ነበረው፡፡ ስለዚህም የግቢ ሚንስቴር ባለስልጣን ነበረ፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቶችን በራሱ ፈቃድ በቦንድና በብድር ከውጭና ከውስጥ ምንጮች በመበደር የሚደግፍ ብቸኛ ሥልጣን ያለው የከተማ መንግስት እንደነበረ ምህረት አየነው (The city of Addis Ababa: Policy option for the Governance and management of a city with Multiple Identity, FSS) በማህበራዊ ጥናት መድረክ ባቀረበው ጽሑፍ ላይ ይገልጻል፡፡ ጽሑፉም ሲቀጥል ከ1966 በኋላ የማዘጋጃ (የከተማ አስተዳደር) ሉዓላዊነትና አስተዳደር በጊዜው የፖለቲካ ሁኔታ ተጽእኖ ምክንያት አጥቷል፡፡ የከንቲባዎች እና ኃላፊዎች ሹመት የገዢው ፓርቲ አባልነትን የሚጠይቅና በማዘጋጃ ቤት ለመቀጠር እንደ ቅድመ ሁኔታ የሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ እስከ 1989 ድረስ አዲስ አበባ በአብዛኛው ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነች ቻርተር ከተማ ነበርች፡፡ ከ1983 ኢህአዴግ ከመጣ በኋላ ከተማዋ ለፌዴራል መንግስት ዋና ከተማ፣ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ እና የነዋሪው ሉዓላዊ ፍላጎት ማስተናገጃ በመሆን ብዙ ጠያቂ ማንነት ያላት ከተማ ሁናለች ይላሉ በአማራጭ ማቅረቢያ ጽሑፋቸው፡፡

ሌላኛዋ ከአዲስ አበባ የባሰችው መከረኛ ከተማ ድሬዳዋ ስትሆን በኦሮሚያው ኦህዴድና በሱማሊያው-ሶህዴፓ ለዓመታት በይገባኛል ንትርካቸው የተነሳ በሦስተኛ ወገን እንድትተዳደር ከተወሰነ ዘመናት አልፈዋል፡፡ የሶማሊያና የኦሮሚያ ክልሎች ወደየክልላቸው ይዞታ እንዲካለል በወቅቱ አንስተውት የነበረው ጥያቄ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያገኝ ከ1985 ጀምሮ ለፌዴራል መንግስት ተጠሪ ሆኖ የቆየ ከተማ መሆኑን የድሬዳዋ ቻርተር መግቢያ ያስረዳናል፡፡ ተጠሪነቷ ለፌዴራል ሁኖ መሪዎቿን ኢህአዴግ ይሾምላታል፡፡ ከንቲባ ኦህዴድ ሲሆን ምክትሉ ሶህዴፓ፣ ሶህዴፓ ፕሬዝዳንቱን ሲያጭ ኦህዴድ ተከታይ እየሆነ የማዘጋጃ ቤት አስፈጻሚነቱን ተከፋፍለው ይነርቷታል፡፡ መሠል ውዝግቦችን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚወሰን ህገመንግስቱ የሚያስገድደው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስካሁን ጉዳዩን አልመከረበትም፡፡ ከኮንትሮባንድ ንግድ መከልከል በኋላ ምጣኔ ሀብቷ ተንኮታኩቶ ባለችበት ስትረግጥና ነዋሪዎቿ በተመልካች እጦት ሲቆዝሙ አምተዋል (ዓመታት አስቆጥረዋል)፡፡ ዳንኤል ብርሐኔ አዲስ ነገር ላይ በጻፈው ድሬዳዋና እና የፌዴራሉ ብዥታ ባለው ጽሑፍ “ድሬዳዋ እንደ አዲስ አበባ ለጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት፣ ለኢንቬስተሮች፣፣ ለፓርቲዎችና ለጋዜጦች ያልተቋረጠ ትኩረትና ዕገዛ የታደለች አይደለችም፡፡ ድሬዳዋ ልታካክሰው የሚገባት በርካታ የባከኑ ዓመታ እና የዞረ ድምር አለባት” ይላል፡፡ እርግጥም ድሬዳዋ የብዙሓን ሕብረተስብ ክፍል መኖሪያ እንደመሆኗ ከሚያዋስኗት ኦሮሚያና ሶማሌ ክፍለ ግዛት ነጻ ወጥታ የይገባኛሉ ጥያቄ እልባት እስኪያገኝ ራሷ በራሷ ልታስተዳደር በቻርተር ከተማነት መለየቷ እንደቤል አፍአዊ እይታው ሥጦታ የሚያስብል ነበር፡፡ ምንም እንኳ የከተማዋ ዕጣ ፈንታ ገና ያልታወቀ ቢሆን፡፡ ይኸው አስርት አመታ አልፈዋል፡፡

Horn affair ድረ ገጹ ላይ ዳንኤል ብርሃነ የጻፈው የ40-40-20 መርሐግብር ያለውን የድሬዳዋ ወቅታዊ ሁናቴ አመላካች ይሆናል፡፡ በ2006 መግቢያ ላይ በኢህአዴግና በሶህዴፓ መካከል በተደረገ የመከፋፈል ውል መሠረት 40% የሥልጣን ኃላፊነትን ለሶህዴፓ የቀረው ለኢህዴግ ማለትም 40% ለኦህዴድና 20% ለቀሩት ሶስት የኢህዴግ ፓርቲዎች (ህወሃት፣ ብአዴን፣ደህዴን) ይከፋፈላል፡፡ የዚህ ውል ውጤትም የድሬዳዋን ከንቲባ በሶህዴፓና ኦህዴድ ኢህአዴግ መሐከል ለማዟዟር በተስማሙት መሠረት የመሪ ልውውጥ ይደረጋል፡፡ ዳሩ እንደ 2007 ሕዝብ ቆጠራ መሰረት የ40-40-20 ጥርቅም የሕዝብ ብዛትን መሠረት ያደረገ አልነበረም፡፡ 40% ኦሮሞ፣ 25% ሶማሌ፣ 20% አማራ እና 14% ሌላ ብሔር ስብስብ ያለባት ነችና፡፡

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት-መንግስት የመሠረቱት ዘጠኝ ሉዓላዊ ክልሎች (መንግስታት) እንደሆኑ በአንቀጽ 47 ላይ ዘርዝሮ አስቀምጧቸዋል፡፡ ሁለቱ መስተዳደር ከተሞች የኢትዮጵያን መንግስት ለመመስረት ሉዓላዊ ሥልጣን የላቸውም እንደማለት ነው፡፡ ሕገመንግስቱ አዲስ አበባን እንደ ዋና ከተማነቷ በሚያወሳበት አንቀጹ ለሶስት ጌቶችን እንድትገዛና ባለቤት የሌላት ከተማ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ አንድም ዋና ከተማ ስትሆን የአስተዳደሩ ተጠሪነት ለፌዴራሉ በማድረግ ያልተገደ ሥልጣን ሰጥቶ ፣ በኦሮሚያ ክልል ስለመገኘቷ ለኦ/ብ/ክ/መንግስት ልዩ መብት እንዳለው በመደንገግ እና ነዋሪዎች ያላት ከተማ እንደመሆኗ በሕዝቦቿ ነጻ ፍላጎት እንድትመራ በሦስት ችንካር ቀንድዶ ይዟታል፡፡(የኢ/ህገመንግስት አንቀጽ 49)

ድሬዳዋን ህገመንገስቱ ጨርሶ የማያውቃት ከተማ ነች፡፡ ድሬዳዋን የፌዴራል ግዛት ለማድረግም ሆነ ራሷን የቻለች ክልል አድርጎ ለማቋቋም ህገ መንግስታዊ መሠረት የለም፡፡ ስለዚህም ድሬ ዳዋ እኔ ባይ አስተዳዳሪ የሌላት የሶማሊያ፣ የኦሮሚያና የፌዴራል ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ አገዛዝ ከነዋሪዎቿ የነጻነት ትግል ጋር የምትቆዝም ነዋሪ እንጂ ባለቤት የሌላት ከተማ ሆናለች፡፡

ሁለቱም መስተዳድሮች ሲቋቋሙ በቻርተር በመሆኑ ህገመንግስታቸው ይኸው ያቋቋማቸው ቻርተር ነው፡፡ ሉዓላዊነታቸውን የሚያቀዳጅና ነጻነታቸውን የሚያስር ቻርተር መሆኑ ነው፡፡ ያለምክንያት አይደለም እንዲህ ማለታችን፤ ለእማኝነት የሚበቃውን የኤርምያስ ለገሠን የመለስ ቱርፋት መጽሐፍ አጣቅሰን በየመስተዳድሮቹ ቻርተር ለማስረገጥ ስለሚቻለን ነው እንጂ፡፡

የአዲስ አበባ የመጀመሪያው 87/1989 ቻርተር የተሻለ ነጻነትና ሉዓላዊነት ለከተማው ሕዝብ የሰጠ ነበር፡፡ ሆኖም ከቀደመው ቻርተር አፈጻጸም የተገኙትን ተሞክሮዎች በማጤን በማለት የተሻሻለውን ቻርተር አረቀቁ፡፡ የ361/1995 ቱ የአዲስ አበባ እና የ416/1996 የድሬዳዋ ቻርተር ግን የ1992 ምርጫ ውጤት በፈጠረው ፍራቻ የ1997 ምርጫን አሻግሮ በማየት ሊመጣ ያለውን በመፍራት አስቀድሞ የተዘጋጁ ሰነዶች ናቸው፡፡ የመንግስትን ሥልጣን መቆጣጠሪያና የሕዝብን ሉዓላዊነት ማረጋገጫ የሆኑት ሦስቱ የዲሞክራሲ አለባዎችን እነኚህ ሰነዶች እንዴት እንደደፈጠጧቸውና ለመንግስት የሕዝብን ሉዓላዊነት የሚሻማ ስልጣን እንዳወረሳቸው ለማስረዳት በተናጥል እንመልከታቸው፡፡

የሕግ አውጪነት ሥልጣን(legislative power)

በሁለቱም ህገ መንግስት (ቻርተር) ላይ የየከተሞቹ ህግ አውጪ አካል በነዋሪዎቿ ይሁንታ አግኝቶ የተመረጠ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ እሰየው! ይህ ታላቅ ነጻነትን ለህዝቡ መስጠትና ሉዓላዊነትን ማጎናጸፍ ነው፡፡ ዳሩ ብዙም ሳይሄድ እነኚህ በነዋሪው ፈቃድ የተመረጡ ህግ አውጪ አካላት (ምክር ቤት) ተጠሪነታቸው ለፌዴራል መንግስት ነው ይላል፡፡ለፌዴራል መንግስት ተጠሪነት ብቻም ሳይሆን የፌዴራል መንግስት ምክር ቤቱን በፓርላማ መበተን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ (የአ/አ ቻርተር 17፥1-2፣የድ/ዳ ቻርተር 15፥1-2፣ የኢ/ ህገ መንግስት አንቀጽ 49÷3)እንደውም በግልጽ ሲያስረዳን በ(የአ/አ 61፥5-6፣ የድዳ 51፥2-3) ላይ “የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስተር የፌዴራልን መንግስት በመወከል የከተማውን አስተዳደር ሥራ ይከታተላል፡፡ ….. የከተማው አስተዳደርም እቅዱን፣ በጀቱንና የከተማውን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ ዓመታዊና ወቅታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀርባል”ይላል፡፡ በግልጽ በከተማው ሕዝብ የተመረጠ ህግ አውጪ አካል ለፌዴራሉ አስፈጻሚ መስሪያ ቤት ተጠሪነት የሚሰጥ ህግ መሆኑ ነው፡፡ የሚከታተለውንና የሚያባርረው የመረጠው ሕዝብ ሳይሆን የፌ/መንግስት ከሆነ ታዲያ የሕዝቡ ተወካዩን መምረጡ ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው?“ይህ ከሕዝቦች ሉዓላዊነት ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ የከተማው ሕዝብ ሉዓላዊነት ተረጋግጧል የሚባለው ነዋሪዎቹ የመጨረሻውን የወሳኝነት ሥልጣን ባለቤት ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ የሕዝቦች ሉዓላዊነት እየተለካ የሚሰጥ ሳይሆን ከራሱና መራጩ ሕዝብ የሚመነጭ ነው፡፡ በተጨባጭ የታየው ግን የየከተሞቹ ህዝብ የሚያስተዳድሩትተወካዮች የሚመርጥበት፣ ሲያሻው ደግሞ የሚሽርበት ስርዓት መጣሱ ነው፡፡ አዲስ አበባ [ድሬዳዋ]ማለት ዜጋ የሆኑ ነዋሪዎቿ ናቸው፡፡ እነዚህ ነዋሪዎች ባለሙሉ ሥልጣንና የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት በመሆናቸው ማንም ይህን መብት ሊነጥቃቸው አይችልም” (ኤርምያስ ለገሠ, ገጽ. 21)

የህግ ተርጓሚ(judicial power)

አንደኞቹ የህግ መተርጉማን ፍርድቤቶች ቢሆኑም፤ በተለየ ውድድር ሳይሆን ከየክልል ም/ቤቶች አባላት በህዝብ ብዛት በሚወከሉት አባላት የሚዋቀረውና በዓለም ላይ የሌለ ሥልጣን ባለቤት የሆነው (ኤርምያስ ለገሠ, ገጽ. 19) የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሌላኛው የመተርጎም ስልጣን የተሰጠው ነው፡፡ የፌዴሬሽን ም/ቤት ኢትዮጵያ ዳኞቿ ህገመንግስት የመተርጎም መብት ስለሌላቸው አንድን ህግ ህገ መንግስታዊ ነው አይደለም ብሎ የመወሰን ሥልጣን እና የበጀት ማከፋፈያ ቀመር በመስራት ለአባል ክልልሎች ድጎማ ይሰጣል፡፡ (የኢ/ ህገ መንግስት አንቀጽ 61 እና 62) ሁለቱም ከተሞች የክልልነት ሥልጣን ስለሌላቸው ቢያንስከ ስድስት የማያንስወንበር በፌዴሬሽን ምክር ቤት አጥተዋል፡፡ በመሆኑም ህጋዊ የሆነው የቀመር ስሌት ውስጥ የሉበትም ስለዚህም የሚያገኙት ድጎማ የለም፡፡ ከ አምስት ሚሊየን የሚበልጠው የአዲስ አበባ ሕዝብም ሆነ ከግማሽ ሚሊየን የማያንሰው የድሬዳዋ ሕዝብ አንድን በሃገሪቱ የወጣ ህግ ህገ መንግስታዊ ነው ህገ መንግስታዊ አይደለም ብለው የመወሰን ድርሻ የላቸውም፡፡

የህግ አስፈጻሚነት ሚና(executive power)

የሁለቱም ከተሞች ሕዝቦች ከንቲቦቻቸውን (ፕሬዝዳንቶቻቸውን) በተናጥል የመምረጥ እድል እንደሌላቸው “ከንቲባው ተጠሪነቱ ለከተማው ም/ቤትና ለፌዴራል መንግስት ነው”በማለት ተቀምጧል፡፡(የአዲስ አበባ ቻርተር 21፥1፣ የድሬዳዋ ቻርተር አንቀጽ 20) ከንቲባውና የካቢኔ አባላት ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በኢህአዴግና አጋር ድርጅቶች የሚመደቡ ናቸው፡፡ (ኤርምያስ ለገሠ, ገጽ. 5፣ 16) ስለሆነም መዲናይቱ ሆነች ድሬ ዳዋ ለዓመታት የሚተዳደሩት በምስለኔ ፕሬዝዳንቶችና ከንቲባዎች ሆኗል፡፡

የየከተሞቹ የፖሊስ ኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነሮች የሚሾሙት በከንቲባው ሳይሆን በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስተር እንደሚሆን ቻርተራቸው ያትታል፡፡ የከተሞቹ ፖሊስ ኮሚሽንም ተጠሪነቱ ለከተማው ሕዝብ ሳይሆን ለፌዴራል ፖሊስ እንዲሆን መሰጠቱን ይገልጻል፡፡ አስቂኙ ነገር ለከተማው ሕዝብ በቀጥታ ተጠሪ ያልሆነው ይህ ተቋም አጠቃላይ በጀቱ፤ ደመዎዙን ጨምሮ የሚመደበውና የሚከፍለው የከተማው ነዋሪ ነው፡፡ (የአዲስ አበባ ቻርተር 27፥ቁጥር 1እና 1 ለ፤ ቁጥር 2፣ የድሬዳዋ ቻርተር 26፥ ቁጥር 1-ሀ እና ሐ እና ቁጥር 2)ኤርምያስበመለስ ቱርፋቶች መጽሐፉ ይህን ጉዳይ ሲዳስስ የ97 ምርጫ ትዝታውን እንዲህ አስቀምጦልናል፡፡

“ከ97 ውጤት በኋላ በአዲስ አበባ ኢህአዴግ እንዴት ይቀጥል የሚለውን ለመወሰን ከተቋቋመ ሦስት አጥኚ ቡድን አንደኛው በአርከበ እንቁባይ የሚመራው ቡድን ይህንን ጠብቆ እንዲፈነዳ የተዘጋጀ አንቀጽ በማጣቀስ አማራጭ ሀሳብአ ቅርቦ ነበር፡፡ ቅንጅት መዲናይቱን በተረከበበ ሁለት ዓመት ውስጥ የተለያዩ አመጾችን በማስነሳት ፀጥታውን መቆጣጠር አልቻሉም ብለን የከተማውን ም/ቤት በፓርላማ እንበትነው የሚል፡፡ የሚገርመው ቅንጅት ሊወነልበት የተዘጋጀው የፀጥታ ችግር ለእሱ ተጠሪ ካልሆነው ከፖሊስ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነበር፡፡”(ኤርምያስለገሠ, ገጽ. 21)

ሌላው የተነፈገው የአስተዳደር ሥልጣን ደግሞ የገንዘብ ምንጭ መደፈን ነው፡፡ የየከተሞቹ አስተዳደር የፌዴራል መንግስት ካልፈቀደላቸው በስተቀር ከሃገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮች መበደርም ሆነ የዋስትና ሰነዶች በመሸጥ ለመበደር እንደማይችሉ ቻርተራቸው አግዷቸዋል፡፡ የአዲስ አበባው አስተዳደር ዓለም አቀፍ የገንዘብ ምንጮችን አፈላልጎቢያገኝ’ኳ የሚበደርለት ፌዴራል መንግስት ብቻ ነው (የአዲስ አበባ ቻርተር 54፥1 እና 3፣ የድሬዳዋ ቻርተር አንቀጽ 45)፡፡ አስቀድመን እንዳልነው በሌላ በኩል እነኚህ ከተሞች እንደሌሎቹ ክልሎች በህግ በተደነገገና በቀመር የተሰላ ድጎማ ከፌ/መንግስት ማግኘት አይችሉም፡፡ የፌዴራል መንግስት በራሱ መልካም ፈቃደኝነት ብቻ እንደአስፈላጊነቱ የፋይናንስ እገዛ ሊያደርግ ከመቻሉ በቀር፡፡ በከተማው ከሚኖሩ ግለሰብ ነጋዴዎችና ከተማዎቹ ባለቤት ከሆኑባቸው ድርጅቶች የተጨ.እ.ታክስ በፌ/መንግስት ብቻ ይሰበሰባል፡፡ (የአ.አ ቻርተር 52፥5 የድ.ዳ ቻርተር 43፥5) በመሆኑም ቻርተራቸው ከተሞቹ ከገንዘብ አንጻርም እግር ከወርች በማሰር እያሽመደመደ የፌዴራሉ ፍርፋሪ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ህዝቡም ከፌዴራሉ መንግስት የስንዴ መና ጠባቂ ሁኗል (ኤርምያስ ለገሠ, ገጽ. 6)፡፡ የባለቤት አልባ መጽሐፍ ደራሲ የ1997 ምርጫ ትረካም እንዲሁ ይቀጥላል፡፡

“በ97 በሕዝብ ፍላጎት የተመረጡት ቅንጅቶች አስተዳደሩን ቢረከቡት (እንኳንም አልተረከቡ!) እንደፈለጉት ወስነው ከተማዋን ከተዘፈቀችበት አረንቋ ሊያወጧት አይችሉም ነበር የተባለበት ሌላኛው ምክንያት ይህ ነበር፡፡ የፌ/መንግስቱ ከሀገር ውስጥ ፋይናንስ ተቋማት እንዲበደሩ እንደማይፈቅድላቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ፌዴራል መንግስት ከውጭ ተቋማትእንዲበደርላቸው መጠየቅም አፍን ከማበላሸት አያልፍም፡፡ የፌ/መንግስቱ በሕግ የሚገደድበት የድጎማ ሥርዓት በሌለበት ሁኔታ እጁን ፈታ አድርጎ በተቃራኒው ለቆመው ከተማው አስተዳደር መና ይወረውራል ብሎ መጠበቅ ማሞ ቂልነት ነው፡፡ አስተዳደሩ የሚያመነጨው ገቢ ደግሞ እንኳን ትላልቅ ካፒታል ፕሮጀክቶችን ሊሠራ ቀርቶ የሠራተኛ ደመዎዝና መደበኛ ወጪዎችን ለመሸፈን በየዓመቱ የሚንገታገት ነው፡፡”አስተዳደሩ ለፌ/መንግስት እንዳለው ተጠሪነትም “እነ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶክትር ሽፈራው ጋር እየሄዱ ስለልማታዊ መንግስት፣ የሥርዓቱ አደጋዎች ስለሆኑት ጠባብነትና ትምክህት፣ ስለአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርሆዎች፣ ስለኪራይ ሰብሳቢነት የአቅም ግንባታ ትምህርት ይወስዱ ነበር ማለት ነው? ወይንስ …. በየወሩ እየቀረቡ ‘ክቡር ሚኒስተር! ይህን አድርገናል፣ በጀታችን ይህን ያህል ነው፤ የከተማው አጠቃላ ሁኔታ ደግሞ ይህን ይመስላል…. ክቡርነትዎ የሾሙልን የፖሊስ ኮሚሽነርና ም/ኮሚሽነር አላሰራ አሉን እባክዎ ይቀይሩልን!!’ የሚል ተማጽኖ ያቀርቡ ነበር?” (ኤርምያስ ለገሠ, ገጽ. 22እና 23)

ይባስ ብሎም በእንቅርት ላይ እንዲሉ በ1997 በተካሄደው ምርጫና ውጤት የተነሣ በአቶ መለስ ቀጭን ትዕዛዝ ቁልፍ የአዲስ አበባ ገቢ ማስገኛ ዘርፎች፤ የከተማው ውልና ማስረጃ እንዲሁም የአንድ ከተማ የደም ሥር ተደርገው ከሚቆጠሩት አንዱ የሆነው የትራንስፖርት ክፍል እንደተቀማ ፤ የአንበሳ አውቶቡስ ሳይቀር ተጠሪነቱ ለፌ/መንግስት እንደሆነ እንዲሁም ለዚህም አቶ መለስ “የቅንጅት ፈረሶች የሆኑትን የከተማ ታክሲዎች ከጨዋታ ውጭ ሳናደርግ ውሳኔው አይቀለበስም” የሚል ምላሽን የከተማው ነዋሪ ቅሬታ እንዳለው በተናገሩበት ስብሰባ ወቅት እንደሰጣቸው አቶ ኤርምያስ ጨምሮ ጽፏል፡፡

በከተሞች ላይ ቦግድርግም ሲል የሚታየው የቁስ አካል (physical) ልማት እንኳ የፌ/መንግስት አስገዳጅ ስሜትን ሲከተል የኖረ ነው፡፡ ለውጥ እንዲፈጥር አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር ከተሞቹ እዛው ይረግጣሉ፡፡ መንግስት ለአዲስ አበባ ባቡር ለመገንባት እስከዛሬ የት ነበረ ቢባል ዛሬ ስለተገደደ እንጂ አስቦና አቅዶ ያመጣው ልማት አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ እንግዲህ ኢህአዴግ እንደሚለው የብዙሐን ፓርቲ ሥርዓት በሐገሪቷ ስላለ ተቃዋሚዎቹም ሊቀናቀኑት ይሮጣሉ የት ውስጥ እንደሚያስገባቸው ግን አስቀድሞ የሚያውቀው እርሱ ነው፡፡ እኛም የሁለቱ ከተሞች ነዋሪዎች እጃችንን ከምርጫ ኮሮጆ ከመሰንዘር አንታቀብም ይስሙላው ሳይገባን፡፡ መነሻችን የቤል ቻርተር ከተማነት ጉዳይ ሁኖ ሁለቱን ከተሞች አነሳን እንጂ ተቃዋሚዎች የሚወዳደሩት መፈናፈኛ የሌለው ሥልጣን ላይ እንደሆነ በየክልሉ የተዘረጋ ሥርዓት ያስረዳናል፡፡ ስለዚህም መሠረታዊ ለውጥ እንጂ ግማሽ የሚባል ሥልጣን ለውጥ እንደማያመጣ መረዳት ይቻለናል፡፡ ምርጫ የሚፈጥረው ፓርላማ በቁጥር መግባትን ይሆናል፡፡ ይኼ ደግሞ ለውጥ እንደሌለው ለ24 ዓመታት አይተነዋል፡፡ የአየነውን መረዳት በአእምሮአችን ስንፈጥር ሥልጣኑን በእጃችን እናስገባለን፡፡

እንደ ኢህአዴግ ፖለቲከኞች ብልጣብልጥነት የቤል ፖለቲከኞችም እንዲሁ ነበር ያደረጉት ለሕዝብ ጥቅም የመጣ የሚመስል መዋቅርና ሃሳብ- ቻርተር ከተማ!! ኢህአዴግ እንዲህ አይደል ያለው “እኛ ለሕዝብ ከጠቀመ የርዕዮተ-ዓለም አምላኪ አይደለንም..[ትንሽዬ ማስተካከያ ላድርግ.. ለሥልጣን ላይ ቆይታ የሚረባ ከሆነ..]… ሶሻሊዝም በሉት አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግስት በሉት ልማታዊ ዲሞክራሲ…[አላሉም እንጂ ወደፊት ሊብራልም ሳይጨመር አይቀርም … .. ያው ዓለም ላይ ያለው ርዕዮት የሚያልቅ ከሆነ ማለቴ ነው]”(አቶ ጻዲቅ በፋና ራዲዮ የኢህአዴግ ተከራካሪ) የቤል ታሪክ በቻርተር ከተማነት መቀየር ብቻ አያበቃም የምርጫ ወጋቸውም እንጂ -የቤል ታሪክ ይቀጥላል ይቆየን!

 

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑